የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 43 "ማንም ሰው ከሕግ ውጭ ሕይወቱን ፣ ነጻነቱን እና ንብረቱን መነጠቅ አይችልም "በማለት ይደነግጋል ።በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 43 ድንጋጌ መሰረት ለሰው ልጅ ሕይወት ፣ ነፃነት እና ንብረት ተገቢውን የህግ ጥበቃ እና ከለላ ይደረግለታል ማለት ነው ።ይህንን የሕገ መንግሥታችን ድንጋጌ የጣሰ ወንጀለኛ ስለሆነ ለሕግ መቅረብ ይኖርበታል ።
ይህንን የሕገ መንግሥታችን ድንጋጌ እንዳነሳው ያስገደደኝ ጉዳይ በዚህ በአገራችን በደቡብ ኢትዮጵያ ከሀዋሳ ከተማ ጀምሮ እስከ ኦሮሚያው ጠረፍ ከተማ ሞያሌ ድረስ ያለው የትራንስፖርት እጥረት እና ከታሪፍ በላይ መክፈል ከቁጥጥር ውጭ መሆን የተገልጋዩን ህብረተሰብ ለቀን ወሮበሎች እየዳረጋቸው ነው ።
በአሁኑ ጊዜ ከሀዋሳ ከተማ ጀምሮ እስከ ሞያሌ ድረስ ያለው መንገድ በመሰራት ላይ ስለሚገኝ መንገዱ ተበላሽቶ ለትራንስፖርት አመቺ አለመሆኑ እንዳለ ሆኖ በዚህ አጋጣሚ የተከሰተው እጥረት እና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል ከላይ የጠቀስኩትን የሕገ መንግሥታችን ድንጋጌ የጣሰ በመሆኑ ህዝቡ የመንግሥት አለህ ጩኸታቸውን የሚሰማ ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል ።
ከሀዋሳ ከተማ እስከ ሞያሌ ድረስ ያለው ርቀት 490 ኪሎ ሜትር ስሆን የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ወገኖች በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውን የትራንስፖርት ታሪፍ ውጭ ብር 400 (አራት መቶ) እያስከፈሉ ነው ።
ከሀዋሳ 98 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚትገኘው ድላ በታሪፉ ብር 26.34 የነበረው በአሁኑ ሰዓት ብር 70 (ሰባ)፣ ከድላ ከተማ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚትገኘው ቡሌሆራ(አገረማርያም)በታርፉ 30(ሰላሳ)የነበረው በአሁኑ ጊዜ የትራንስፖርት ታሪፍ ብር 120(አንድ መቶ ሃያ)ብር ሆኗል። ከቡሌሆራ እስከ ሞያሌ ያለው ርቀት 300 ኪሎ ሜትር ስሆን በታርፉ ብር 340(ሦስት መቶ አርባ)እንድንከፍል እየተገደድን ነው።
የዚህ ከታሪፍ ውጭ ማስከፈል ምክንያት ምን እንደሆነ አንዳንድ ሹፌሮች እና ረዳቶቻቸው ስናገሩ "የነዳጅ መጥፋት እና የመንገድ መበላሸት ነው" ይላሉ ። የሕግ የበላይነት የሰፈነበት አገር ውስጥ አገልግሎት የሚሰጠው አካል ለሚሰጡት አገልግሎት ልከፈላቸው የሚገባ ክፍያ እንዲሁም አገልግሎት የሚፈልጉ ለሚፈልጉት አገልግሎት መክፈል የሚገባቸው ክፍያ በመመሪያ እና በዝርዝር ተቀምጦ እያለ አሁን በደቡብ ኢትዮጵያ የተከሰተው የታሪፍ በላይ መክፈል ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል ።
ለዚህ ለተከሰተው የትራንስፖርት እጥረት እና ከታሪፍ በላይ መክፈል መንሰኤው
1 ከሀዋሳ ከተማ ጀምሮ እስከ ሞያሌ ድረስ ያሉት መስመሮች በሁለት የተለያዩ ክልላዊ መስተዳደሮች ማለትም በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በመተዳደራቸው የእነዚህ ሁለቱ ክልላዊ መንግሥታቶች ተቀራርቦ እና ተደጋግፎ አለመስራታቸው ።
2 በእየስምርት ጣቢያ ላይ የተመደቡ ሠራተኞች የተሰጣቸውን ሃላፊነት መሸከም የማይችሉ እና ለሕዝቡ ጥቅም መከበር የማይሠሩ ደንታ ቢሶች መሆን ።
3 በሁለቱም ክልል የሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ፣ ሹፌሮች ፣ ረዳቶች ፣ የትራፊክ ፖሊሶች ፣ የመንገድ ትራንስፖርት ቁጥጥር የተሰማሩ የከተማዎቹ ሹማምንቶች ፣ የእየክልሎቹ ባለስልጣናት የህብረተሰቡን ችግር ለመስማት አለመፈለጋቸው በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡባዊ ኦሮሚያ እየታየ ላለው ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ለመጣው የትራንስፖርት እጥረት እና ከታሪፍ በላይ መክፈል እንድከሰት መንስኤ ነው ።
ይህ በዚህ አከባቢ የተከሰተው የትራንስፖርት እጥረት እና ከታሪፍ በላይ መክፈል በአከባቢው ብቻም ሳይሆን በሙሉ በአገርቷ የኑሮ ውድነት ፣ የሕግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ መግባት ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ከዚያም በላይ በአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ የማይቀር ጉዳይ በመሆኑ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት እና በተዋረድ የሚገኙ የእየክልሎቹ ባለስልጣናት አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ ካልወሰዱ ህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ተሟጦ ቦኋላ ውጤቱን ለመገመት አዳጋች የሚሆን አመፅ እና ብጥብጥ ልያስከስት ሥለሚችል ከወዲሁ ቢታሰብበት መልካም ነው እላለሁ ።
በቸር ሰንብቱልኝ
Wellcome to the official blogger page of getachewbulti. This is getachewbulti official blogger page. Dedicated to posting my ideas,pictures, videos & vines of ethiopian's to show off our beauty and culture contributions are Wellcome.
Sunday, 15 February 2015
ሰሚ ያጣው የሕዝቡ ጮኼት!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment